Sunday, 24 March 2024 00:00

የአይበገሬነት ጽናት፡- ከመሳዳ አምባ እስከ መቅደላ አምባ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ወቅቱ እ.ኤ.አ 73 ዓ.ም.፣ ስፍራው ደቡብ እስራኤል። በመሳዳ አምባ ምሽግ ላይ በጅምላ መስዋዕትነት የተደመደመው የአይበገሬነት ፅናት በመላው ዓለም ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ ናኘ። የኃያላን ኃያል የነበሩት ሮማውያን እየሩሳሌምን በጭካኔ ሁኔታ ሲወሩ፣ 967 አይሁዳውያን አመፁ። “በባርነት አንገዛም” ብለውም ራሳቸውን መከላከል ወደሚያስችላቸው የመሳዳ አምባ ሸሽተው መሸጉ። ውሎና ሰንብቶ ሽንፈት አይቀሬ ሲሆን ደግሞ እጅ ከመስጠት ይልቅ በህብረት ራሳቸውን እስከ ወዲያኛው ለማጥፋት መረጡ። ለጭቆና አልበገር ባይ የሆነው የጀብደኝነታቸው ተምሳሌትነት፣ ዘመናትንና አህጉራትን አቋርጦ ተደመጠ። እንደ ገደል ማሚቶ ከአድማስ እስከ አድማስ አስተጋብቶም፣ በሌላ የአምባ ምሽግ ላይ በተመሳሳይ መልኩ በ1860 ዓ.ም. ተደገመ - በመቅደላ አምባ ኢትዮጵያ!

የሁለት አምባ ምሽጎች ወግ
ታሪክ በፈታኝ ሁኔታ ቢሆን እንኳ አልገዛም ብለው ጀብድ በሚፈፅሙ ጀግኖች ታሪክ የበለፀገ ነው ይባላል። ይህን መሰል ጀብድ ከተፈፀመባቸውና የአምባ ምሽግን ተገን ካደረጉ አስደናቂ ስፍራዎች መሀል የእስራኤሉ መሳዳን እና የኢትዮጵያው መቅደላን መጥቀስ ይቻላል። በመልክዓ ምድራዊ ስፍራቸው የትየለሌ ቢሆኑም፣ ሁለቱ የአምባ ምሽጎች የተጋሩት የእምቢተኝነት ገድል ልክ በአለት ላይ ተጠርቦ እንደተፃፈ ታሪክ ሁሉ ዘመን ተሻጋሪ ነው።
የመሳዳ አምባ ምሽግ ለጉዞ አስቸጋሪ በሆኑ በልሙጥ ገደሎች የተከበበ ስፍራ ነው። እ.ኤ.አ ከ66-73 ዓ.ም. በተካሄደው የአይሁድና የሮማ ጦርነት ወቅት ለአይሁድ ተፋላሚዎች ተፈጥሯዊ ጋሻና መከታ ሆኖ አገልግሏል። ለሮማውያኑ ጦረኞች እንደ ግድግዳ ቀጥ ያለውን ዳገት መወጣጣት እጅግ ፈታኝ ነበር። ለተከላካዮቹ ደግሞ ረዘም ላለ ወቅት አሌ የማይባል ጥቅም አስገኝቶላቸዋል። ሆኖም ሮማውያን ከእስራኤል የማረኳቸውን ብዙ ሺህ ባርያዎች አስገድደው ከመሳዳ ሥር ባለ በአንድ ጉብታ ላይ የመረማመጃ ክምር በማስከመራቸው፣ አይደፈሬው የመሳዳ አምባ ምሽግን በተሻለ ብቃት ለማጥቃት ችለዋል። ይህ ቦታ በመጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ ባይጠቀስም ዳዊት ከሳኦል ሸሽቶ (1ኛ ሳሙ 23፡ 14) የኖረበት ሳይሆን አይቀርም ይባላል።
በፅናት የተቆመባቸው የአምባ ምሽግ አምዶች
ልሙጥ ባለ ገደል የተከበበውን የመሳዳን አምባ ተገን በማድረግ አይሁዶች ለበርካታ ወራት የሮማውያንን ጥቃት በጀግንነት መክተው ነበር። ሆኖም ግን የአምባው ምሽግ መገርሰስ አይቀሬ እየሆነ መጣ። ቢሆንም የተዋጊዎቹ የመንፈስ ጽናት ፍንክች አላለም።
ይህ የተጋድሎ ታሪክ አህጉር አቋርጦ እና ሺህ ዓመታትን ተሻግሮ ራሱን በኢትዮጵያ ደገመ። የሀገር ውስጥ ተቀናቃኞች ከአውሮፓውያን ወራሪ ጦር ጋር ተረዳድተው፣ አጤ ቴዎድሮስን ጦርነት የገጠሟቸው ከመቅደላ አምባ ምሽጋቸው ነበር። ይህ ከፍ ያለ ጠረጴዛማ ስፍራ ለዝንጀሮ እንኳ በሚያዳግት መልኩ ዙሪያውን ጭው ባለ ገደል የተከበበ ነው። ከላዩ ላይ ከተወጣ በኋላ ግን ሰፊና ሜዳማ ነው። እዚህ ስፍራ ላይ ነው እንግዲህ አጤ ቴዎድሮስ ተፈጥሮን፣ ሴባስቶፖል መድፋቸውንና ጀግንነታቸውን አቀናጅተው በጄኔራል ናፒየር የሚመራውንና ዘመናዊ ጦር መሣሪያ የታጠቀውን 32,000 የአንግሊዝ-ህንድ ሰራዊት ሊመክቱ ያደፈጡት።

አይበገሬው የመቅደላ አምባ ምሽግ
መቅደላ አምባ በገደላማነቱ የሚኮራና ተፈጥሯዊ የመከላከያ ጠቀሜታን የተጎናፀፈ ነው። አጤ ቴዎድሮስ በጋፋት ያሰሩትንና ክብደቱ ከ8,000 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝነውን የሴባስቶፖል መድፍ በጋሪ ጭነው ከ320 ኪሎ ሜትር አስቸጋሪ ምድርና ሽፍቶች ጋር እየታገሉ፣ ከስድስት ወር ተኩል በላይ በማጓጓዝ ከአምባው በመድረስ የምሽጉን አቅም አፈርጥመዋል።
በተፈጥሮ አቀማመጧ ሳቢያ የመቅደላ አምባ በአስተማማኝ የወታደራዊ ምሽግነትና  ያመጠኛ ወንጀለኛ እስረኛ ማስቀመጫነት ትታወቃለች። በተለይም አጤ ቴዎድሮስ በስተመጨረሻው የሥልጣን ዘመናቸው መቅደላ አምባን እንደ ዋና መዲናቸው አድርገው ይቆጥሯት ነበርና በርካታ ውድ ንብረታቸውን የማስቀመጫ ስፍራ አድርገዋት ነበር። በተጨማሪም ዳግማዊ ምኒልክ ገና ልጅ ሳሉ በአጤ ቴዎድሮስ ተወስደው በ1857 ዓ.ም እስከ አመለጡበት ወቅት ድረስ ለዐስር ዓመታት በዚሁ በመቅደላ አምባ ምሽግ ተወስነው እንደቆዩበት ይታወሳል።

የጋራ እንቢተኝነት ትሩፋት
ምንም እንኳ የመሳዳ እና የመቅደላ አምባ ምሽጎች በመልክዓ ምድራዊ ስፍራና ጠባያቸው እጅግ ቢለያዩም፣ ጭቆናን በመቋቋም ረገድ ጥልቅ በሆነ አይበገሬነት መንፈስ የተጋመዱ ናቸው። ፍፃሜው ቢያሳዝንም በሁለቱም የአምባ ምሽጎች የተመረጠው መፍትሄ እጅ መስጠት ሳይሆን የሞትን ፅዋ በክብር መጎንጨት ነበር።

የነጻነት ተዋጊዎቹ ልብ ሰባሪ ምርጫዎች
ምንም እንኳ እውነትነቱን ጥያቄ ውስጥ ያስገቡ ጸሐፍት ቢኖሩም፣ በጉብኝቱ ስፍራ ላይ የሚነገረው ታሪክ እንዲህ ነው። የመሳዳ አምባ ምሽግ አለቆች እያንዳንዱ የአይሁድ ባል ሕይወቱን ከማጥፋቱ በፊት ሚስትና ልጆቹን እንዲገድል ኃላፊነት ተጣለበት። በውጤቱም ቁጥራቸው ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ የመሳዳ አማፂያን ራሳቸውን በራሳቸው በማጥፋት (ማስ ሱይሳይድ) ሮማውያኑ በስተመጨረሻ እጃቸውን በመያዝ ሊያገኙ የሚችሉትን ርካታ ነፍገዋቸዋል። በተመሳሳይ መልኩ በመቅደላ አምባ ምሽግም አጤ ቴዎድሮስ ለእንግሊዝ ወራሪ ጦር እጅ ከመስጠት ይልቅ በገዛ ሽጉጣቸው የመስዋዕትነትን ፅዋ በጀግንነት ተጎንጭተዋል።

ትሩፋትን ማዝለቅ
የመሳዳ አምባ ምሽግ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ታሪካዊ ስፍራ ሲሆን፤ ለአይሁድ ሕዝብ የዓላማ ፅናት ለቀጣይ ትውልድም ሆነ ለመላው ዓለም ጉልህ ማሳያ ሆኗል። ጎብኚዎች የአርኪኦሎጂ ቅሪቶችን ማየት ብቻ ሳይሆን አማፂያኑን የመጨረሻውን የሞት ፅዋ የተጎነጩበት ስፍራ ላይ ቆመው ታሪክን የኋሊት እንዲመለከቱ ተመቻችቶላቸዋል። ወደ ተራራው አናት በሚያደርስ የገመድ ላይ ተንጠልጣይ ትራንስፖርት በመጠቀም ጎብኚዎች ሙት ባሕርን ጨምሮ አስደናቂ የሆነ ዙሪያ ገባውን መቃኘት ይችላሉ፤ ለስፍራው ከፍተኛ የገንዘብ ጥቅምም ያስገኛሉ።
ባንፃሩ ምንም እንኳ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙም ባይታወቅም የመቅደላ አምባ ምሽግ ተመሳሳይ የተጋድሎ መስዋዕትነት የተከወነበት ድንቅ ስፍራ ነውና ተገቢው እውቅና እና ክብር ሊቸረው ግድ ይላል።

ከመቅደላ አምባ የምንማራቸው
ከአጤ ቴዎድሮስ መስዋዕትነት ጋር ተያይዞ አራት አንኳር ትምህርትን መቅሰም ይቻላል። ቁርጠኛ ፍላጎት ካለ አገርን ለማሳደግ የሚያስችል እቅድ በማቀድ ወደ እድገት ጎዳና በፍጥነት ማቅናት መቻሉን፤ አገራዊ ሉዓላዊነትን ከባዕድ ወረራ ለመግታት በጽናትና መስዋዕትነት የመቆም አስፈላጊነትን፤ የውጭ ጠላትን ከመጋፈጥ አስቀድሞ አገር ውስጥ ካሉ ተፎካካሪዎችም ሆነ ባላንጣዎች ጋር ልዩነትን አቻችሎና ተባብሮ አለመሥራት የሚያስከትለው መዘዝን፤ እንዲሁም የኅይል እና የጭካኔ አገዛዝ ጠቀሜታው ለጊዜው ብቻ እንጂ ዘላቂ አለመሆኑን ነው።
ችግርን ለመጋፈጥ የማይናወጥ ፅናትና ጥንካሬ እጅግ አስፈላጊ ቢሆንም ገደብ ያልተበጀለት አምባገነንነት የሚያመጣው አደጋ ደግሞ የትየለሌ ነውና፣ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ርዕሰ ብሔር ደረጃ ላይ ያሉ ባለሥልጣናት ልብ ሊሉት የሚገባ ተሞክሮ ነው።
የድርጊት ጥሪ
በመጪው ሚያዝያ ሰባት ቀን ለሚከበረው 156ኛው የመቅደላ ጦርነት መታሰቢያ በዓል እየተቃረብን ነው። እግረ መንገዳችንን አምባው እንደ ማሳዳ ሁሉ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ የተባበሩ ጥሪ ቢደረግ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። አንደኛ፣ የታሪካዊነቱን ፋይዳ ስፋትና ጥልቀት በእጅጉ ያልቀዋል። ሁለተኛ፣ ከቃጠሎ ተርፈው እንግሊዝ ውስጥ በብሪቲሽ ሙዚየምም ሆነ በሌሎች ስፍራዎች የሚገኙትን በመቶዎች የሚቆጠሩ የተዘረፉ የባህል ቅርሶችን አንድ በአንድ እየለመኑ በመቀበል ሳይሆን ሁሉንም ባንድነት ለማስመለስ የፈረጠመ ጫናን ይፈጥራል። (እዚህ ላይ በርካታ የተዘረፉ ቅርሶችን በማስመለስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማትን ሳንዘነጋ ነው)። ሶስተኛ፣ በአሁኑ ሰዓት መቅደላ ላይ በሚያሳዝን መልኩ በጥቂት የድንጋይ ካቦች ብቻ በምልክትነት የሚታየው የአጤ ቴዎድሮስ መቃብርም ሆነ ሌሎች ታሪካዊ ክንውን የተፈፀመባቸው ስፍራዎች ለጎብኚዎች በምቹ ሁኔታ ቢጎለብቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሊገኝ የሚችለው ኢኮኖሚያዊ ትሩፋት ለአካባቢውም ሆነ ለሕዝቡ እድገት በጎ ሚና ይጫወታል።
የአጤ ቴዎድሮስ እና የመቅደላ አምባ ጀብድ በበርካታ ዕውቅ ቲያትሮችና ቱባ ተዋንያን፣ በታሪካዊ መጻሕፍት፣ በሥዕሎች፣ በዘፈኖች፣ በፖለቲካ ዲስኩሮች፣ ወዘተ ደምቀው መወደሳቸው የሚያስመሰግን ተግባር ነው። ነገር ግን ውዳሴና አድናቆቱ የላቀ ትርጉምና ጠቀሜታ የሚያስገኘው ጉዳዩ ወደ መሬት ወርዶ በስፍራው ላይ ሲታይና ሲጨበጥ ነው። ለዚህ ተግባር ደግሞ አምባውን በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የማስመዝገቡ ጥረት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ይህ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም፤ እስካሁን አለመደረጉ በእራሱ ዘግይቷልና።
***
ከአዘጋጁ፡-
* ዳንኤል ካሳሁን (ፒ ኤች ዲ) በተለያዩ ከባቢያዊ ነክ ጉዳዮች ዙሪያ በጂኦግራፊያዊ ምልከታና የጥንቅር ዘዴ ተመርኩዘው፣ መጣጥፎችን በተለያዩ የሕትመት ውጤቶች  ለኢትዮጵያውያን ያካፍላሉ። ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻቸው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 873 times